St. Michael Ethiopian Orthodox Church Columbus Ohio
  • Home
  • About
  • Services and Calendar
  • News and Articles
  • Contact

Timiket - Epiphany- ጥምቀት

1/16/2017

0 Comments

 
የጥምቀት በዓል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በተላይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባህር የተጥመቀበትን ዕላት የሚያስታውሰው ኤጵፋንያ በመባልም የሚታወቀው ደማቅ በዓል ነው።

​የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ታሪክ በማቴ 3፥13-17 ላይ ይገኛል

በሃገራችን ጥር 10 ቀን በከተራ ታቦታት ከየ አቢያተ ቤተክርስቲያንቱ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ በምዕመናን ታጅበው በዝማሬና በልልታ ይሄዳሉ። ሲደርሱም በተዘጋጀው ድንኳን እንዲያርፉ ተደርጎ ሌሊቱን እዚያው ያሳልፋሉ ። በከተሞች ሰው ሰራሽ ግድብ ሲዘጋጅ በገጠር ወደ ወንዞች በመሄድ ይከበራል።፡ምክንያቱ ደግሞ ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን ለማመልከት ነው። ጥር ፩፩ ቀን ይጥምቀት ዕላት በገጠር ጎኅ ሲቀድ ምዕመናን በድንኳኑ ስር (ዙሪያ) አስቀድሰው ሲጨርሱ በካህናት መሪነት ሁሉም ወደ ወንዙ ያመራሉ ውሃው ይባረካል ህዝቡም በጸበሉ ተረጭቶ(ተጠምቆ) ወደ ዝማሬው ይመለሳሉ። “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደመሪታዊ” ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ የሚለው የዕለቱ ቀለም በሊቃውንቱ አንደበት በያሬዳዊ ዜማ ጎልቶ ይሰማል የዘመራል። ከዚህ ስነስርዓት በኋላ ህዝቡ በዝማሬና በልልታ ካህናቱ በሃሌታ በከበሮን በጽናጽል ታቦተ ህጉን አጅበው እንደአመጣጣቸው ወደ መንበራቸው ወደየ አብያተ ክርስቲያናቱ ይመለሳሉ።
 በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ቤተክርስቲያናችን ከቤተ መቅደስ ውጭ ከምታከብራቸው በዓላት አንዱና የመጀመሪያው ነው። ልክ እንደመስቀል በዓል ማለት ነው። ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው በየጥምቀተ ባህሩ የመከበሩ በመሆናቸው ሀገሬው ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብ በመፍጠሩ ጥቁርና ነጭ ያለምዘር ሁሉ እንዲያከብረው ሆኗል ዛሬም እኛ በዚህባለንበት ምድረ አሜሪካ ስናከብር ሁሉን የሚስብ የሚማርክና የተለያየውንና የተበታተነውን ህዝብ አንድ የሚያደርግና የሚያቀራርብ ይሆናል ብለን እናምናለን የካህናቱና የምዕመናኑ ሀገርኛና ሃይማኖታዊ አለባበስም ፍጽም ይማርካል። ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን ያለው ጊዜ ዘመነ አስተርዮ በመባል ይታወቃል። በዚህ ግዜ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ሚስጢር የተገለጠበት በመሆኑ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሰርግ ላይ የመጀመሪያው ተአምር በኢየሱስ ክርስቶስ መደረጉና አምላካዊ ኃይሉን መግለጡ እየታሰበ ምስግስንስ ይቀርባል። ስለሆነም ዘመነ አስተርዮ ተብሎ ይጠራል። ዮሐ 2-1 በኢትዮጵያ አኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓል ሃይማኖትን ከባህል አስተባብራ ስለምታከብረው ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲኖረው ሆኗል።

ጥምቀት ምንድ ነው?
    ጥምቀት ማለት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ ማለት ሲሆንቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት መነከር መዘፈቅ መጥለቅ ማለት ነው ጥምቀት ከሰባቱ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን አንዱና መድኃኒ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐ 3-5 ላይ እውነት እውነት እልኃለሁ ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም። ብሎ እንደተናገረው ከውሀና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የሥላሴ ልጅነት የምናገኝበት መንግስተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢያታችን የሚደመሰስበት ድህነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምስጢር ነው። ጥምቀት በምስጥረ ሥላሴና በሚስጥረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢያት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሄርን መንግስት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው።

የጥምቀት አመጣጥ የጥምቀት መስራቹ ራሱ መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፌት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢያት ሥርየት(ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው ይሄውም እግዚአብሔር በረዴት የሚገልጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔርር ቢት መገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ የማጠብ የማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር። የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሰራር ነበር። ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ወደ ተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድሞው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው ሰውነታቸውን ከአፋዊ ወይም ከውጫዊ እድፍ በማጠብና ንጽህ በማድረግ በባህርይው ንጹህና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹህ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምስጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር። 
   
አሮንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባችዋልህ በውሃም ታጥባቸዋለህ ዘሁ 29-4
   ሙሴም አሮንና ልጆቹን አቀረበ በውሃም አጠባቸው ዘሌ 8-6

የጥምቀት ምሳሌዎች በብሉይ ኪዳን

አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከ ጸዲቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፤ አብርሃም የምዕመናን መልከ ጸዲቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው። ዘፍ 14-17

ኢዮብ በዮርዳኖስ ተቀምቆ ከደዌው ተፈውሷል። ይህም ምዕመናንተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው። ንዕማን ሶርያዊ ተጠምዎ ከለምጹ ድኗል 2ኛ ነገ 5-14 የኸውም ምዕመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ይየመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፤ የኖህ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ናት ዘፍ 6-13 ይኽንንምሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውሃ የዳኑባትን መርከብ ሲሰራ በኖህ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዛገዬ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው። አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል። ሥጋን ከእድፍ በመታጠብ አይደለም ክርስቶስ በመነሳቱእግዚአብሔርን እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ 1ኛ ጴጥ 3-20  እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባህርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው። ዘፀ 14-15 ይህንንምሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደጋረዳቸው ሁሉም በባህር መካከል አልፈው እንደሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ። ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባህር አጠመቃቸው። 1ኛ ቆሮ 10-1

ለአብርሃም ህግ ሆኖ የተሰጠው  ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው። አብርሃም ካረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዝዞ ነበር። ዘፍ 17-9 “በሰው እጅ ያልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁተገርዛችሁ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብላችኋል በእርስዎም ከሙታን ለይቶ ባስነሳው በእግዚአብሔር ረዳትና በሃይማኖት ከርሱ ጋር ተነስታችኋል። ቆላ 2-11 ጌታ ለምን ተጠመቀ ለትሕትና ለትምህርት ለኛ አርአያ ለመሆን ዮሐ 13-1-17

የእዳ ደብዳቤያችንን ሊቀድ ሊደመሥ ቆላ 2-14 የሦስትነትን ምስጢር የገልጽ ዘንድ ማቴ 3-16 በጥምቀቱ ጥምቀታችንን ለመባረክ ተጠመቀ።

ለምን በ30 ዓመቱ ተጠመቀ?
በብሉይ ኪዳን ሥራዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልዕኮና መንፈሳዊ አገልግሎት ክ30 ዓመት እድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር እጅግ አስፈላጊ እንኳን ቢሆን ክ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በእድሜና በእውቀት የበሰሉ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ህዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው። ዘፀ 4-3 1ኛ ዜና መዋ 23-24 1ኛ ጢሞ 3-16-10 ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው ብ30 አመቱ ነበር። ይፕሐንስ መጥምቅ የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ዳርቻ በይሁዳ ምድረበዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜ በኋላ ነው።ሌላው ዓቢይ ምክንያት የሰው ሁ መጀመሪያው የሆነው አባታችን አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ኦኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶ ኋላም በኃጢያት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለመመለስ ነው። የጌታ መጠመቅ ውሃውን ለመቀደስ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው። ጌታ ተጠምቆ ከውሃ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ይህ የምወደው ልጄ ነው ብሎ ሲመሰክርለት የሚስጥረ ስላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል። ማቴ 3-16


በዮሐንስ እጅ ለምን ተጠመቀ?
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትህትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው። ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ብሎት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ነገስታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ

ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው። ጌታ ስሆን በባርያዬ(በአገላጋዬ) ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም። ምክንያቱም እርሱ እከበር አይል ክቡር እጽድቅ አይል ጽድቅ ነውና።

ለምን በዮርዳኖስ ተጠመቀ?
​በኢየሩሳሌ አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው ። ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፤”ባህር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ። መዝ 11 3-3 ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት(በመገረዝና ባለመገረዝ) ተለያይተው የነበሩ ህዝብና አህዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ ነሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል ያመኑ የተጠመቁ መዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግስተሰማያትን ይወርሳሉ።

ለምን በሌሊት ተጠመቀ? በኃጢያት ጨለማ ስለነበር ህዝብ የጽድቅ ብርሃን እንዲወጣለትና በጨለማ የሚመሰል ኦሪት ይኖር ስለነበረ ለህዝብ ብርሃን የሂነ ወንጌል መገለጡን ልማሳየት ነው። ኢሳ 9-2 አንድም ጌታ ልደቱ ጥምቀቱ ትንሳኤው እንዲሁም ምጽአቱ በሌሊት ነው። ይህም ዮሆነበት ምክንያት ሌሊቱን ተከትሎየሚመጣው ብርሃን በመሆኑ ከሞት ወደ ህይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት ከሃጢያት ወደ ጽድቅ የመሸጋገሪያችን ምሳሌ ነው።
ለምን በውሃ ተጠመቀ?
ጌታ የሁሉ ነገር አስገኝ መሆኑ ይታወቃል ከውሃ ይልው የከበሩና የተወደዱ ነገሮች ነበሩ ልምሳሌ ወተት የማርጠጅ የመሳሰሉ ነገሮች ነበሩ በእነዚ ነገሮች አልተጠመቀም ለምን? ቢባል ሁሉም በእኩልነት የሚያገኘው ድሃውም ሀብታሙም ባልስልጣኑም ተራው ህዝብም በነጻ ያለ ዋጋ የሚገኝ ስለሆነ በውሃ ተጠመቀ በወተትና ብሌሎች ነገሮች ተጠምቅቆ ቢሆን ኖሮ ሳንቲም የሌለን መግዛት የማንችል ድሆች የጥምቀቱ ተከፋዮች መሆን ይከብደን ነበር ስለ ዚህ ቀለል ባለና በሁሉም ቤት በሚገኝ ውሃ ተጠመቀ።

                               ይቆየን ።
                               አዘጋጅ፡ መጋቤ ምስጢር ቀ. ውድነህ 

0 Comments



Leave a Reply.

Powered by Create your own unique website with customizable templates.
  • Home
  • About
  • Services and Calendar
  • News and Articles
  • Contact